አብዛኛው ሰው ሁለት ኩላሊቶች ይኖሩታል። ነገር ግን ከ750 ሰዎች መካከል አንዱ አንድ ኩላሊት ኖሮት ይወለዳል። ሁኔታው በወንዶች ላይ ጎላ ብሎ የሚታይ ቢሆንም ብዙም ሊያሳስብ የሚገባ ጉዳይ አይደለም፤ ምክኒያቱም አንድ ጤነኛ ኩላሊት ያለ ምንም ችግር የሁለቱንም ቦታ ሸፍኖ መስራት ይችላል። በዚህም ምክኒያት አንድ ኩላሊት ያላቸው ሰዎች መደበኛ ሥራ፣ ጉልበት የሚጠይቅ ሥራ ለመስራትም ሆነ የፆታ ግንኙነት ለማድረግ አይቸገሩም።
በዚህም ምክንያት ከውልደት ጀምሮ አንድ ኩላሊት ያላቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ያላቸው አንድ ኩላሊት እንደሆነ የሚታወቀው ለሌላ ህመም አልትራሳውንድ፣ ራጅ ወይንም ሲቲ ስካን ሲነሱ ነው። ነገር ግን በአንዳንድ ሰዎች ላይ ከብዙ አመታት በሗላ የደም ግፊት እና ፕሮቲን ንጥረ ነገርን በሽንት እንደማጣት አይነት ችግሮች ይስተዋላሉ። የኩላሊት አቅም መዳከም ግን ብዙ የሚስተዋል ችግር አይደለም።
ምክንያቶቹ ምንድን ናቸው?
- ከላይ እንደተጠቀሰው ከ750 አንድ ሰው ከውልደት ጀምሮ አንድ ኩላሊት ብቻ ይኖረዋል።
- እንደ ካንሰር፣ ጠጠር፣ መግልና አደጋ ባሉ ምክንያቶች በቀዶ ጥገና አንዱ ኩላሊት ሲወጣ
- ኩላሊት ለሚያስፈልገው ሰው በሚለገስበት ጊዜ
ለምን ጥንቃቄ መውሰድ ይኖርብናል?
ሁለት ኩላሊት ያላቸው ሰዎች የአንዱ ኩላሊታቸው አቅም ቢዳከም በሌላኘው መጠቀም ይችላሉ። አንድ ኩላሊት ያላቸው ሰዎች ግን ይህ ዕድል የላቸውም። በዚህም ምክንያት አንዱ ኩላሊት ላይ የሚያጋጥም ችግር በቶሎ የኩላሊት ስራ መዳከም እና ማቆም ሊያመጣ ይችላል።
በቶሎ የኩላሊት ስራ ማቆም ለተለያዩ ችግሮች ሊያጋልጥ ስለሚችልና ህይወትን አደጋ ላይ የሚጥል እክል በመሆኑ፤ ህሙማን በአፋጣኝ የኩላሊት እጥበት ህክምና ማግኘት አለባቸው።
ለጉዳት የሚያጋልጡ ሁኔታዎች?
- ከሽንት ቧንቧ በላይ ያሉ ቱቦዎች ላይ በአጭር ጊዜ ሸንት እንዳያስተላልፉ እንደ ጠጠርና የረጋ ደም ባሉ ነገሮች ሲዘጉ
- በሆድ ዕቃ ላይ የሚደረጉ ቀዶ ጥገናዎች ላይ በሚከሰት ከሽንት ቧንቧ በላይ ያሉ ቱቦዎች መቆረጥ አደጋ ሽንት ወደ ፊኛ እንዳይተላለፍ ስለሚያረግ ወደ ኩላሊት በመመለስ ያለችው አንዱት ኩላሊት ላይ የባሰ ጫና ሊፈጠርና ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።
- እንድ ኩላሊት ብቻ በሚኖርበት ጊዜ ከሰውነት ጋር የተመጣጠነ ስራ ለመስራት ኩላሊቱ በመጠን እና ክብደት ይጨምራል። ይህ ደግም የሰውነት ነክኪ እና ግጭት የሚበዛባቸው እንደ ማርሻል አርትስና ቡጢ ያሉ ሰፖርታዊ ዉድድሮች ፤ በሚደረግ ጊዜ ለጉዳት የበለጠ ተጋላጭ ያደርገዋል።