የኩላሊት ህመም ምልክቶች ከሰው ወደ ሰው ይለያያሉ። መሰረታዊ የህመሙ ዓይነት እና እንደ ከባድነቱ የሚታይብት የህመሙ ምልክት ይወሰናል። ምልክቶቹ ብዙውን ጊዜ ፣ ግልጽ ያልሆኑ እና አስደንጋጭ ያልሆኑ ናቸው። ስለሆነም በህመሙ የመጀመሪያዎቹ ደረጃዎች ህመም ስለመኖሩ ለመለየት አዳጋች ነው።
የኩላሊት ህመም በተለምዶ የሚታዩ ምልክቶች
የፊት ፣ የሆድ እና የእግር እብጠት ብዙ ጊዜ የኩላሊት ህመም ማሳያ ነው። በኩላሊት ህመም ምክንያት የሚከሰት እብጠት አንድ ባህሪይ በመጀመሪያ ከዐይን ሽፋኖቹ በታች የሚስተዋል መሆኑ ነው (ይህ የፔሪኦሮቢታል እብጠት ይባላል) እና በማለዳ በጣም ጎልቶ መታየቱ ነው። ነገር ግን እብጠት የግድ የኩላሊት መጎሳቆልን እንደማያመለክት ልብ ልንለው ይገባል። በተወሰኑ የኩላሊት ህመሞች ውስጥ መደበኛ የኩላሊት ሥራ ቢኖርም እብጠት ይከሰታል (ለምሳሌ ኔፍሮቲክ ሲንድሮም)። ከዚህም ጎን ለጎን መረዳት የሚያስፈልገው ከባድ ህመም ቢከሰትም በአንዳንድ ታካሚዎች ላይ እብጠት ላይታይ እንደሚችል ነው።
-
የምግብ ፍላጎት ማጣት ፣ ማቅለሽለሽ ፣ ማስመለስ
የምግብ ፍላጎት ማጣት ፣ በአፍ ውስጥ ያልተለመደ ጣዕምና የምግብ መመገብ ደካማነት የኩላሊት ችግር ያለባቸው ሰዎች የሚያጋጥማቸው የተለመዱ ችግሮች ናቸው። የከፋ የኩላሊት ድክመት በሚኖርበት ጊዜ የማቅለሽለሽ ፣ ማስመልስ እና የአእምሮ ህመም የሚያስከትሉ መርዛማ ንጥረነገሮች መጠን እየጨመረ ይሄዳል።
የኩላሊት ችግር ያለባቸው ታካሚዎች ብዙውን ጊዜ የደም ግፊት ይኖራቸዋል። የደም ግፊት ችግር በወጣትነት ዕድሜ (ከ 30 ዓመት በታች) ከተገኘ ወይም በምርመራው ወቅት የደም ግፊት በጣም ከፍተኛ ከሆነ ምክንያቱ የኩላሊት በሽታ ሊሆን እንደሚችል መጠርጠር ያስፈልጋል።
ቶሎ መድከም ፣ ማተኮር አለመቻል እና የቆዳ መገርጣት የደም ማነስ ችግር ያለበት ሰው የተለመዱ ምልክቶች ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ሥር የሰደደ የኩላሊት መድከም የመጀመሪያ ደረጃዎች ላይ አንድ ሰው የሚያሳያቸው ብቸኛ ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ። የደም ማነስ ያለበት ሰው በመደበኛ ህክምና በተለምዶ በሚሰጡ መድኃቶች ካልዳነ፣ የኩላሊት ህመም እንዳለበት መጠርጠር ያስፈልጋል።
ከዚህም ተጨማሪ ምልክቶች -ዝቅተኛ የጀርባ ህመም ፣ አጠቃላይ የሰውነት ህመም ፣ እና የእግር ማሳከክ እና ህመም በኩላሊት ህመም ውስጥ ተደጋጋሚ የሚታዩ ምልክቶች ናቸው። በደንብ አለማደግ ፣የቁመት ማጠር እና የግር አጥንት ቀጥ አለማለት በልጆች ላይ የኩላሊት ህመም የሚያሳይ ነው።
የተለመዱ ምልክቶች
- በሽንት መጠን መቀነስ ፣ በተለያዩ የኩላሊት ህመሞች ውስጥ በጣም የተለመደ ነው።
- ሽንት በሚወገድበት ወቅት የሚያቃጥል ስሜት ፣ በተከታታይ መሽናት (ያልተለመደ ድግግሞሽ) እንዲሁም ደም ወይም መግል በሽንት ውስጥ ማየት የሽንት ቧንቧ ህመም የሚያሳዩ ምልክቶች ናቸው።
- የሽንት ፍሰት መዘጋት ሽንትነn ለማስተላለፍ ችግር ያስከትላል።
ምንም እንኳን አንድ ሰው ከላይ ከተዘረዘሩት ምልክቶች መካከል የተወሰኑት ሊያሳይ ቢችልም የግድ ሰውዬው በኩላሊት ህመም ተይዟል ማለት ግን አይደለም። ሆኖም እንደዚህ አይነት ምልክቶች ባሉበት ሁኔታ ሀኪምን ማማከር እና የኩላሊት ህመም እና ሌሎች ህመሞች መኖር ወይም አለመኖራቸውን በደም እና በሽንት ናሙና ምርመራዎች ማረጋገጥ የግድ ይላል።